ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ ቀጣናዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እያጠናከረ ነው - ሚኒስትር ማርቲን ኤሊያ ሎሙሮ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የፓን-አፍሪካኒዝም ጠንካራ እሳቤ ቀጣናዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እያጠናከረ መሆኑን የደቡብ ሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ማርቲን ኤሊያ ሎሙሮ ገለጹ።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ከሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት በሁለትዮሽና ቀጣናዊ የትብብር መስኮች ላይ መክረዋል።

የደቡብ ሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ማርቲን ኤሊያ ሎሙሮ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የትብብር መስኮች ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ዲፕሎማሲያዊ ውይይትም የሀገራቱን የትብብር አድማስ በማስፋት ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላምና ደኅንነት የምታበረክተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሀገራቱን ወዳጅነት በጠንካራ መሰረት በማነጽ ሁለንተናዊ የትብብር አቅሞችን እያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንገድ መሠረተ ልማትና በኃይል አቅርቦት ሀገራቱን ለማስተሳሰር የሚደረጉ ጥረቶችም የኢኮኖሚ ትስስርን በማጠናከር በህዝብ ለህዝብ ትስስር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የመሰረተ ልማት ትስስር ያላት ቁርጠኝነት ቀጣናዊ የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ከማጠናከር ባለፈ ለደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት የላቀ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ ቀጣናዊ ትስስርን እያጠናከረ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤም የአፍሪካዊያን የአንድነት መተሳሰሪያ ገመድ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም