ወጣቱ ትውልድ ሕብረትና አንድነቱን በመጠበቅ ለሀገር ዕድገት ሊሰራ ይገባል-ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ትውልድ ሕብረትና አንድነቱን በመጠበቅ ለሀገር ዕድገት ሊሰራ ይገባል-ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን
አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-ወጣቱ ትውልድ ሕብረትና አንድነቱን በመጠበቅ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት አበክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ገለጹ።
የካቲት-12 የሰማዕታት ቀን 89ኛ የመታሰቢያ ቀን በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሃውልት እየተካሄደ ነው።
በመርሀ ግብሩ ላይ እናት እና አባት አርበኞችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ጊዜ የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን እንዳሉት፤ ቀደምት አርበኞች በከፈሉት ውድ መስዋትነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት በማስጠበቅ ለትውልድ አስተላልፏል።
የአሁኑ ትውልድም ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ ወቅቱ የሚጠይቀውን የልማት አርበኝነት በመላበስ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የቀደምት አርበኞች ለኢትዮጵያ ነፃነት የከፈሉት አኩሪ ተጋድሎም ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ትምህርት መሆኑን ገልጸዋል።
በየዓመቱ የሚከበረው የሰማዕታት ቀንም ቀደምት አርበኞች ለሀገራቸው በመታመን የከፈሉትን መስዋዕትነት ትውልድ እንዲዘክረው ለማስቻል የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።