ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ በመመካከር ብሔራዊ መግባባት የሰፈነበት ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ይችላሉ - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ በመመካከር ብሔራዊ መግባባት የሰፈነበት ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ይችላሉ - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ በመመካከር ብሔራዊ መግባባት የሰፈነበት ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት እንደሚችሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
ምክር ቤቱ በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባው፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት ገምግሞ የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን አመልክቷል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ባቀረቡት ዝርዝር ሪፖርት፣ ባለፉት አራት ዓመታት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የተሳታፊዎች ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚሁ መሠረት በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮች፣ በስደት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ የቀድሞ ታጣቂዎች ዘንድ የምክክር መድረኮች መካሄዳቸውን ጠቁመዋል።
በትግራይ ክልልም ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር 17 የቅድመ ዝግጅት ውይይቶች መደረጋቸውን አመልክተው፤ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን መጀመር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይ በትግራይ ክልል የሚካሄደውን ምክክር ማሳካትና አስፈላጊ የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ሀገራዊ ጉባዔውን ማካሄድ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ዋናውን ሀገራዊ ጉባዔ ዕውን ለማድረግ 170 ገለልተኛ የውይይት አመቻቾች የተመረጡ ሲሆን፤ የአጀንዳ ቀረጻውን በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላቱ በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወኑት የምክክር ተግባራት ዘላቂ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ተስፋ ሰጪ በሆነ ምዕራፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚሁ መሠረት፣ የምክክሩ ሂደት ባልተቋጨ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ለልዩነቶች መነሻ በሆኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን አመልክተዋል።
አባላቱ በሰጡት ግብረ-መልስም የሴቶችን ተሳትፎ ማረጋገጥን፣ እስካሁን በምክክሩ ያልተሳተፉ የፖለቲካ ድርጅቶችንና በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ማካተትን በሚመለከት ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሚቀሩ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ሥራዎች የሚከናወኑበትን ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው ጠይቀዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር)፤ ባለፉት አራት ዓመታት
የተከናወነው ሀገራዊ ምክክር የሀገረ መንግሥት ስብራትን መጠገን የሚያስችሉ ስኬታማ ምዕራፎች ማለፉን ገልጸዋል።
ይህ የምክክር ሂደት ኋላቀር የፖለቲካ ሥርዓትን በማስተካከል፣ የተቃና ሀገረ መንግሥት ለመገንባትና በብሔራዊ ጥቅሞችና መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የማይደራደር ትውልድ ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
በአሥራ አንድ ክልሎች፣ በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች፣ በውጭ በሚኖሩ ዜጎችና በተለያዩ የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች ዘንድ የተሳካ የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በትግራይ ክልልም የቅድመ ምክክር መድረኮች ሲካሄዱ መቆየታቸውን በመጥቀስ፤ በቀጣይ በክልሉ ቀሪ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ሥራዎች እንዲሁም የጋራ አጀንዳ የመቅረጽ ተግባራት እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፥ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የእስካሁን ሂደቶች ውጤታማ ምዕራፎች የታለፉባቸው ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህም ቀጣይ ቀሪ የሀገራዊ የምክክር ተግባራትን ለማጠናቀቅ እንዲቻል ለኮሚሽኑ ተጨማሪ የስምንት ወራት ጊዜ እንዲሰጠው ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በማጠቃለያ ንግግራቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል ስኬታማ ጉዞ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በቀሪ የምክክር ተግባራትም እያንዳንዱ ዜጋ ሐሳቡን በነፃነት በማጋራት፣ ሂደቱ በድል እንዲጠናቀቅ የድርሻውን ገንቢ ሚና መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
ኢትዮጵያውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በመመካከር ብሔራዊ መግባባት የሰፈነበት ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት መገንባት እንደሚችሉም ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም፣ በዋናው ሀገራዊ ጉባዔ ላይ ሴቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችል ሥርዓት በኮሚሽኑ መዘርጋቱን ከቀረበው ሪፖርት መረዳታቸውን ጠቁመዋል።
በመጨረሻም በቋሚ ኮሚቴው በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ መሰረት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ ዘመንን ለተጨማሪ ስምንት ወራት በማራዘም በምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።