አዲስ አበባ የአፍሪካውያን መዲና እና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን በተግባር ዳግም አረጋግጣለች - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ የአፍሪካውያን መዲና እና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን በተግባር ዳግም አረጋግጣለች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ሁለቱን ታላላቅ ጉባዔዎች በስኬት ማጠናቀቋ የአፍሪካውያን መዲና እና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ዳግም ያረጋገጠችበት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና መርሃ ግብር አካሂደዋል፡፡
በተጨማሪም ለኡራዔል - አትላስ - ቦሌ መንገድ ግንባታ ስኬት አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትም ተመስግነዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ይህ ስኬት የተመዘገበው በተቋማት መካከል በተፈጠረው የተቀናጀ አሠራር መሆኑን ገልጸዋል።
ለጉባኤዎቹ ስኬት ጉልህ ሚና ለተጫወቱት እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና እንግዳ ተቀባይነት ላስተናገዱ የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ የፌዴራል እና የከተማዋ የጸጥታ ተቋማት እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።
ከጉባኤዎቹ ጎን ለጎን፣ የኡራኤል - አትላስ - ቦሌ መንገድ ፕሮጀክት በስኬት ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ ሌላኛው የከተማዋ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅ የላቀ ሚና የነበራቸውን አካላትን አመስግነዋል፡፡
ጉባኤዎቹ በስኬት መጠናቀቃቸው አዲስ አበባ የአፍሪካውያን መዲና እና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን በተግባር ዳግም ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም መሰል ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሙን ማሳደግ፤ ከተማዋን ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎብኚዎች ይበልጥ ምቹ እና ሳቢ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በምስጋና መርሃ ግብሩ ላይ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።