ከዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን መመከት የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን መመከት የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው
አርባ ምንጭ፤ የካቲት 11/2018 (ኢዜአ)፡-ከዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን መመከት የሚያስችል አቅም እየተገነባ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከመረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ያዘጋጀው የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄዷል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ትግበራ በብቃት በማከናወን ለ2030 ስትራቴጂክ ዕቅድ ስኬት በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተለያዩ ዘርፎች የዲጂታል አሰራር ሥርዓት እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው፣ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶች ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ ናቸው ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ ብልጽግናን በጽኑ መሠረት ላይ ለማኖር ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት አመልክተዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ፣ የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ እንዲሁም አካታች የፋይናንስ ሥርዓት የዲጂታል ኢትዮጵያ ትሩፋቶች ናቸው ብለዋል።
ከዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሳይበር ደህንነት ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችል ጠንካራ አቅም እየተገነባ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሯ ያብራሩት።
የሳይበር ደህንነትን በማረጋገጥ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።
ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ለሚገኘው አመራርና ባለሙያም አስፈላጊውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በማንሳት።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ ለምርታማነት፣ ለኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት፣ ለቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
በክልሉ የአስተዳደር፣ የፍትህ፣ የማዘጋጃ እና የፋይናንስ ተቋማት የዘመነና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ በተደረጉ ጥረቶች ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በዲጂታል የመንግስት አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ቦጋለ ቦሸ (ዶ/ር) ናቸው።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በተሟላ መንገድ ለመተግበርና የሳይበር ጥቃቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመከት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።