ቀጥታ፡

ወለጋ የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ልማት የመቀየር አብነት ሆናለች-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018 (ኢዜአ)፡- ወለጋ አካባቢው፣ በሐሳብና በራዕይ በመምራት፣ የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ልማት የመቀየር አብነት ሆኗል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በይቅርታና በመደመር ዕሳቤ ሰላምን እያሰፈንን ዓይናችንን ገልጠን በመትጋታችን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ የልማት እስትንፋስ ሁሉም ቦታ እየተዳረሰ ነው ብለዋል።

በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል የወለጋ ዞኖችና የተለያዩ ወረዳዎች ዛሬ የተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች ነገን በብዙ የሚያሣምሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በቄለም ወለጋ ዞን ሃዋ ገላን ወረዳ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የለማ የሙዝ እርሻ ኢትዮጵያ ያላትን የውኃ ሀብት በተገቢ መልኩ ከተጠቀመች ምን ያክል መልማት እንደምትችል ያሳየ እንደሆነም ተናግረዋል።


 

የአርጆ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ እንደ ሀገር የተጀመረውን የማዕድን፣ የኢንዱስትሪ እና አጠቃላይ ልማት የሚያግዝ ተደማሪ አቅም መሆን ችሏል ነው ያሉት።

ፋብሪካው ለሲሚንቶ፣ ለብረት እና ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊ ጥሬ ግብአቶችን እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት የኢትዮጵያ የመልማት ዐቅም ተጨባጭ ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት እያዋለች መሆኗ በተግባር የታየበትና የብልጽግናችን አመላካች ነውም ብለዋል።

ከሕዝባችን ጋር ሆነን ልማታችንና ያገኘነውን ሰላም የማስጠበቅ ሥራችንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ባደረግነው የልማት ጉብኝት የወለጋ ሕዝብ ላደረገው ደማቅ አቀባበል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም