ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ ከአየርላንድ የዓለም አቀፍ ልማት እና የዳያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ኒል ሪችመንድ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
በዚሁ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል መደበኛ የፖለቲካ ምክክር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል በቅድሚያ ትኩረት በሚሹ ዘርፎች ላይ የጋራ ስምምነት መደረሱም ተገልጿል።
በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ በመድኃኒት ኢንዱስትሪ እንዲሁም በሰው ኃይል ልማት ጠንካራ አርጋነት መፍጠር የሚያስችል ምክክር አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በማጠናከር ረገድ አየርላንድ እንደ መገናኛ ድልድይ ሆና እንደምትሰራ በውይይቱ ተነስቷል።
ውይይቱ የሁለቱን ሀገራት የንግድ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግርም ነው የተገለጸው።