ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ ልማት ባንክ በቀጣናው ሀገራት መካከል ትብብርንና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ ልማት ባንክ በቀጣናው ሀገራት መካከል ትብብርና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ  እየሰራ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ ልማት ባንክ ዋና ዳይሬክተር ቤናርድ ፖል ሞኖ ገለጹ፡፡

የአፍሪካ ህብረት "እኛ የምንመኛት አፍሪካ" በሚል መሪ ሀሳብ የቀረጸው "አጀንዳ 2063" አህጉሪቱን በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ በፖለቲካ የተዋሃደች እና ዜጎች በሰላም የሚኖሩባት አህጉር ለማድረግ ያለመ ግዙፍ ርዕይ ነው።

ይህም የውጭ እርዳታ ጥገኝነትን በመቀነስ የውስጥ ንግድን ማጠናከር፣ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብና የኢንዱስትሪ እድገትን ለማምጣት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።

አህጉራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስር  ለዚህ ግብ ስኬት ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው የሚገለጸው።

የምስራቅ አፍሪካ ልማት ባንክ ዋና ዳይሬክተር ቤናርድ ፖል ሞኖ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ባንኩ የቀጣናውን የኢኮኖሚ እድገት እና ትብብር ለማፋጠን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ልማት ባንክ (EADB) በቀጣናው ሀገራት መካከል የኢኮኖሚ እድገትን እና ትብብርን ለማፋጠን የተመሰረተ የፋይናንስ ተቋም ነው ብለዋል። 

ለቀጣናው ልማት ወሳኝ በሆኑ የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግ እና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የረጅም ጊዜ ብድር እንደሚያቀርብ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 

በዚህም ባለፉት ዓመታት በታንዛኒያ ለባቡር ሀዲድ ግንባታ፣ በኬኒያ ለንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንዲሁም በዩጋንዳ ለኢንዱስትሪዎች እድገት የተደረገውን ድጋፍ በአብነት ጠቅሰዋል። 

ኢትዮጵያ በኃይል ማመንጨት ረገድ ራሷን ለመቻል የምታደርገው ጥረት ለአህጉሪቱ የኢንዱስትሪ እድገት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ያሉ የኃይል ልማት ስራዎች ሀገሪቷ ቀደም ሲል የጀመረችውን የኢንዱስትሪ ማስፋፊያና የማምረቻ ዘርፍ እቅዶችን ለማሳካት መሰረታዊ ናቸው ብለዋል። 

ያለ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ማሳደግ የማይታሰብ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ እያከናወነች ያለችው ተግባር ለቀጣናው ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። 

እነዚህ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሀገራት በኢነርጂ ዘርፍ ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረጋቸው ባለፈ፤ ለጠቅላላ የልማት ጉዞው እንደ ዋነኛ መሳሪያና አጋዥ ሆነው እንደሚያገለግሉ አስረድተዋል። 

ኢትዮጵያ በኃይል ማመንጨትና በሌሎች የልማት መስኮች ራሷን ለመቻል የምታደርገው ጉዞ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል፡፡ 

አፍሪካ ለምትመኘው የላቀ ዕድገትና የረጅም ጉዞ ስኬት ከአንድነትና ከትብብር ውጭ አማራጭ እንደሌላት ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል። 

በአህጉሪቱ የሚተገበሩ የልማት ስራዎችም አህጉራዊ ትስስርን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለዚህም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መመሥረት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል። 

አሁን ላይ አፍሪካውያን የአንዳቸውን ምርት ሌላኛው የሚጠቀምበት ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን ተናግረው፤ ለዚህም  የኢትዮጵያን የስንዴ ምርት ለአብነት አንስተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም