የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ በመጠቀም ድህነትን በአጭር ጊዜ ታሪክ ማድረግ ይገባናል - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ በመጠቀም ድህነትን በአጭር ጊዜ ታሪክ ማድረግ ይገባናል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018 (ኢዜአ)፡- የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀም ድህነትን በአጭር ጊዜ ታሪክ ማድረግ ይገባናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሣ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምዕራብ ወለጋ ዞን የሚገኘውን የቄጦ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክት መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሣ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ስብራቶችን ለመጠገንና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተፈጥሮና የሰው ሀብትን በአግባቡ ማስተዳደር ወሳኝ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ደማቅ የልማት ስኬት በመብቃት ለጥቅሙ ተካፋይ ለሆነው ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከለውጡ ወዲህ በክልሉ ስብራቶችን ለማከም በሦስት ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተድርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ውሃን በመቆጠብ፣ በመስኖና በፓምፕ በመጠቀም ወደ ስራ ለማስገባት ትልቅ ጅማሮ መኖሩን ጠቁመዋል።
ለም አፈርና ማዕድን በአግባቡ ለመጠቀም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የተፋሰስ ልማት ስራዎች መጠናከራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በክላስተር በማረስና የተለያዩ የልማት ኢኒሼቲቮችን በመተግበር ራስን የመለወጥ ስራ ወጤታማ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ያለንን ሰፊና ወጣት የሰው ኃይል ወደ ስራ ለማስገባት የሥራ ባህልን በሚቀይር መልኩ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የቄጦ የመስኖ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አቅጣጫና ውሳኔ ወደ ስራ ገብቶ ዛሬ ለምረቃ መብቃቱን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ፕሮጀክቱ በአካባቢው ለሚገኘው ሕዝብ ትልቅ ተስፋ መሆኑን ተናግረዋል።
በውሃ፣ በአፈርና ባለን የሰው ሀብት ተጠቅመን በመደመር ዕሳቤ ከተመራን በአጭር ጊዜ ውስጥ ድህነትን ማሸነፍ እንችላለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ የተቀረጹ የልማት ኢኒሼቲቮችን ወደ ተግባር እንዲለውጥና የተጀመሩ ጥረቶችን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
የታዩ አነስተኛ ለውጦችን እንደ መነሻ በመጠቀም ለተሻለ ስኬት መትጋት እንደሚገባና ሕዝቡ ሀብቱን በመቆጠብ ወደ ኢንቨስትመንት በመግባት አዲስ ታሪክ እንዲሠራም አሳስበዋል፡፡