ቀጥታ፡

በክልሉ በጤና ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋት ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው

ጂንካ፤ የካቲት 11/2018 (ኢዜአ)-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጤና ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋት ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በክልሉ በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣትና የታካሚዎችን ደህንነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።

በዚህም የወረቀት አሰራርን በማስቀረት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ፈጣንና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለታካሚዎች መስጠት መጀመሩን ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅትም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር በሁሉም የጤና ተቋማት እንዲተገበር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሰራሩ ደረጃውን የጠበቀና በትክክለኛ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የሕክምና ስህተቶችን ቀድሞ ለመከላከል፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የመድኃኒት አጠቃቀምን ለማሳደግና የጤና ባለሙያዎችን የተጠያቂነት ሥርአት ለመዘርጋት ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በጤና ተቋማት በወረቀት በሚደረግ የታካሚዎች መረጃ አያያዝ የመረጃ መጥፋት ችግሮች ሲከሰቱ እንደነበረና  የጤና አገልግሎቱም የተጓተተ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የተጀመረው ዲጂታል የመረጃ አያያዝ የታካሚዎች የሕክምና መረጃ መጥፋትና በዚህ ምክንያት የሚከሰቱ የህክምና ስህተቶችን ለመቀነስ ማስቻሉን ተናግረዋል። 

ዲጂታል አሰራሩ ለተገልጋዩ ፈጣን የጤና አገልግሎት በመስጠት እንግልትን እያስቀረ መሆኑንም አመልክተዋል።

የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያለመና የጤና ጥራት፣ ደህንነትና ፈጠራ ላይ ያተኮረ መድረክ እንደሚካሄድም አቶ እንዳሻው ጠቁመዋል።

በመድረኩ በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በፈጠራ ሥራዎች ለመፍታትና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም