ቀጥታ፡

የመራጮች ትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በስፋት ሊሰሩ ይገባል -ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፤የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦የዜጎችን የምርጫ ግንዛቤ ለማጎልበትና የመራጮች ትምህርት ተደራሽነት ለማስፋት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች  ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተዘጋጀ የመራጮች ትምህርት ማኑዋል ይፋ ተደርጓል።


 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ተክሊት ይመስል እንደገለጹት፤ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። 

የምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና፣ ዲጂታል የእጩዎች ምዝገባና ሌሎች ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል። 

ጠቅላላ ምርጫውን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም፣ የታዛቢዎች መመሪያ፣ የስነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል። 

የመራጮች ትምህርት ለምርጫ እድሜያቸው የደረሱ ሁሉም ዜጎች እንዲመዘገቡ፣ ድምጽ እንዲሰጡ፣ ከምርጫ ውጤት በኋላ በሰላማዊ ሁኔታ ውጤቱን መቀበል ላይ ያተኮረ መሆኑን አብራርተዋል። 

የመራጮች ትምህርት በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የመራጮች ትምህርት መመሪያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። 

ሲቪክ ማህበራት በመመሪያው መሰረት የዜጎች መብትና ግዴታ፣ በመረጃና እውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያካሂዱ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ገለልተኛና መርህን በጠበቀ መልኩ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የመራጮችን ትምህርት ሀገር አቀፍ ተደራሽነት ለማስፋት  የምርጫ ቦርድ፣ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት በመሆኑ በጋራ የሚከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ገልጸዋል።


 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በመድረኩ የተሳተፉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎችም ዜጎች መብታቸውንና ግዴታቸውን እንዲወጡ ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ እስከ  ድህረ ምርጫ ባለው ሂደት ሚናቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።  

የመስጠት ቻሪቲ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ገነት ዋቅቶላ ዜጎች የመራጭነትን መብትና ግዴታቸውን አውቀው ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሂደት እንዲሳተፉ እንሰራለን ብለዋል።


 

የሴራድ ኢንስቲቲዩሽን ምክትል ኃላፊ ዘምዘም አብዱራህማን በበኩላቸው፤ የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ተሳታፊነት እንዲረጋገጥ እየሰሩ መሆኑን ነው የገለጹት። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም