የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የሕዝቡን ሕይወት እንዲለውጡ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የሕዝቡን ሕይወት እንዲለውጡ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦በወለጋ አካባቢ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናቀው የሕዝቡን ሕይወት እንዲለውጡ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምዕራብ ወለጋ ዞን የሚገኘውን የቄጦ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክት መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወለጋ ባለፉት ዓመታት በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ተገቢውን ልማት ሳያገኝ መቆየቱን አስታውሰው፥ ካለፈው የታሪክ ጠባሳ ወጥቶ ወደ አዲስ የብልፅግና ምዕራፍ መሸጋገር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ የሰላምን ዋጋ በአግባቡ የሚያውቅና በተግባር የሚገልጽ መሆኑንም አንስተዋል።
ሆኖም የጸጥታ ችግር ህዝቡ የተፈጥሮ ሀብቱን አልምቶ እንዳይጠቀም እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸው፥ የተገኙ መልካም ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀምና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ሙሉ ትኩረትን ወደ ልማት ማዞር ያስፈልጋል ብለዋል።
የትጥቅ ትግል መርጠው የነበሩ በርካታ ወገኖች የህዝብና የመንግሥትን የሰላም ጥያቄ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት በመመለሳቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡
ሌሎችም ወደ ሰላም የመጡ ወንድሞቻቸውን ፈለግ በመከተል ወደ ሰላም ጠረጴዛ ሊመጡ እንደሚገባ ጠቁመው ችግሮችን በንግግር፣ በውይይትና በእርቅ መፍታት የኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ባህል መሆኑን አስታውሰዋል።
የወለጋ አከባቢ እምቅ የኢኮኖሚ አቅም እንዳለው ጠቅሰው በአንፊሎ የሚመረተውን ጥራት ያለው ቡና ምርታማነትን በመጨመር ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንጂ ግጭትና መገዳደል አይበጅም ብለዋል።
በተጨማሪም የሆሮ እንስሳትን ለኤክስፖርት በማዋል የህዝቡን ህይወት መቀየር እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ዛሬ የተመረቀው የቄጦ ግድብ ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚያለማ መሆኑን ጠቅሰው ከ10 ሺህ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ማድረጉን እንደ ትልቅ ጅማሬ አንስተውታል።
በትጥቅ ትግል ያሉትን ወደ ሰላም እንዲመጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን ያላቸውን ሚና ማላቅ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የአካባቢው ህዝብ እንደ አብዲሳ አጋ ያሉ በዓለም አስድናቂ ገድል የሰሩ ጀግኖችን ያፈራ መሆኑን በመጥቀስ፣ አሁንም በልማት ታሪክ መስራት እንደሚገባው ተናግረዋል።
በመላው ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ሳይሰሩ የቆዩ የልማት ፕሮጀክቶች በዚህ ዘመን እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፥ የቄጦ ግድብና መሰል የልማት ጠብታዎች ተሰባስበው ትልቅ የለውጥ ወንዝ እንደሚሆኑና የዜጎችን ህይወት እንደሚቀይሩ አፅንኦት ሰጥተዋል።