ሀገራዊ ምክክሩ ለብሔራዊ መግባባትና ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ የላቀ ሚና አለው -የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለብሔራዊ መግባባትና ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ የላቀ ሚና አለው -የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፤የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ለብሔራዊ መግባባትና ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ የላቀ ሚና ያለው በመሆኑ ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ወደ ዋናው የምክክር ጉባኤ ለመግባት የሚያስችል ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።
በአስራ አንድ ክልሎትና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተሳታፊዎችን የመለየትና አጀንዳ የማሰባሰብ ስኬታማ ሥራ በስኬት አጠናቋል።
የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፕሬዝዳንትና የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት አመራር አቶ አላምረው ይርዳው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሀገራዊ ምክክሩ ፋይዳ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ሂደቱ በምክክር የመደማመጥን ባሕል ለማሳደግ፣ የጋራ እሴቶችን ለመቅረጽና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ፓርቲያቸው ለሂደቱ ስኬት የራሱን አሻራ እያሳረፈ እንደሚገኝ ገልጸው፥አባሎቻቸው በምክክሩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
ምክክሩ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት፣የሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ባህልን ለማዳበርና ለዘላቂ ሰላም መሰረት የሚጥል በመሆኑ ለውጤታማነቱ በጋራ እንሰራለን ነው ያሉት።
የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀ-መንበርና የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳሮት ጉምአ፤ ሀገራዊ ምክክሩ የሀገረ-መንግሥቱን መሰረት በማጽናት ረገድ ያለውን ሚና አብራርተዋል።
ሂደቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታትና የዜጎችን አቅም ለጋራ ሀገራዊ ግብ ለማስተባበር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ፓርቲያቸውና ጥምረቱ ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።