የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠቅላላ ምርጫው በንቃት ለመሳተፍ ዕጩዎቻቸውን እያስመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠቅላላ ምርጫው በንቃት ለመሳተፍ ዕጩዎቻቸውን እያስመዘገቡ ነው
ባህር ዳር ፤ የካቲት 11/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ ዕጩዎቻቸውን እያስመዘገቡ መሆኑን ገለጹ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠቅላላ ምርጫው በንቃት ለመሳተፍ ከሚጠበቀባቸው ወሳኝ ጉዳዮች አንዱ ዕጩዎችን ማስመዝገብ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅና የሰጣቸው ፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች ምዝገባን በምርጫው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ከጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በቴክኖሎጂ በመታገዝ እያከናወነ ይገኛል።
በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የዕጩዎች ምዝገባ የካቲት አንድ ቀን 2018 ዓ-ም የሚጠናቀቅ ቢሆንም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ምዝገባው እስከ የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም መራዘሙን ቦርዱ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የምርጫውን ሂደትና አጠቃላይ ዝግጅታቸውን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተቀመጠው የጊዜ-ገደብ መሰረት ዕጩዎችን በማስመዘገብ በምርጫው በንቃት እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል።
ፓርቲዎቹ ሰላማዊ የፖለቲካ አማራጭን በመከተል ምርጫው ሕግና ሥርዓትን በጠበቀ መንገድ እንዲከናወን አበክረን እንሰራለን ብለዋል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ (አዲሃን)ስራ አስፈፃሚ አባል አዲሱ ጉልላት፣ የሀገረ መንግስቱን ግንባታ በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰላማዊ መንገድ ወደ ሥልጣን የመጣ መንግስት የህዝቡን የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ በቀላሉ መፍታት እንደሚችል ጠቅሰው፣7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይህን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲከናወን ፓርቲያቸው በሃላፊነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ፓርቲው በምርጫ በቦርዱ የተቀመጡ የቴክኖሎጂ አማራጮች በመጠቀም እጩዎችን እያስመዘገበ መሆኑንና የምዝገባ ጊዜው መራዘም ያልተመዘገቡ የፓርቲው ዕጩዎችን ለማስመዝገብ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እመቤት ከበደ፤ ፓርቲያቸው በምርጫው ከባለፉት ምርጫዎች በተሻለ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድና በውጤቱም ህዝብና ሀገር እንዲያሸንፉ ፓርቲያቸው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ዕጩዎችን ከማስመዝገብ ባለፈ መራጮች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየሰጡ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ማሕበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሰሜን ኢትዮጵያ አስተባባሪ ሃይለማርያም ብርሃኑ ሃሳብን በሃሳብ በመሞገት ብቻ ሀገርና ህዝብ አሸናፊ የሚሆንበት ምርጫ እንዲካሄድ ፓርቲያቸው ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን እንደሚሳተፍ አስታውቀዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት ዕጩዎቻቸውን ያለምንም ችግር እያስመዘገቡ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የምርጫውን ህዝባዊ ቅቡልነት ለማረጋገጥ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የበለጠ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት (ኢብአ) ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረ-እግዚያብሔር ናቸው።
ፓርቲያቸው ለጠቅላላ ምርጫው ዕጩዎቸን እያስመዘገበ መሆኑንና በምርጫው ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በጋራ ምክር ቤቱ በኩል ለመፍታት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።