ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙኃን ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማነት የምርጫ ሕጉንና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን በተከተለ መልኩ በመዘገብ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ገለጸ፡፡ 

መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ወቅት ሙያዊ ስነ ምግባርን የተከተለ አሳታፊና አካታች የሆነ ዘገባ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝቧል፡፡

በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የስትራቴጂክ ጉዳዮች አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት ደጀኔ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ፈቃድ የወሰዱ ከሦስት መቶ በላይ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡

ባለስልጣኑ ለመገናኛ ብዙኃን ፈቃድና እድሳት መስጠት እንዲሁም ተቋማቱ ፈቃድ በወሰዱበት መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ የመከታተልና የመደገፍ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የሚዲያ ተቋማት  ዘገባዎች ሙያዊ ስነ ምግባርን የተከተለና የሀገሪቱን ሕግ ያከበረ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ባለስልጣኑ የድርሻውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ መገናኛ ብዙሃን የድርሻቸውን እንዲወጡ ከማስቻል ረገድ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን የምርጫ ህጉንና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን በተከተለ መልኩ የመዘገብ ኃላፊነት እንዳለባቸው በማንሳት፥ ለዚህም ባለስልጣኑ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እየሠጠ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ባለስልጣኑ የሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

ሙያዊ ስነ ምግባርን ማረጋገጥ የባለስልጣኑ ቁልፍ ተግባር መሆኑን አንስተው፤ በምርጫ ጊዜ መገናኛ ብዙኃን ሙያዊ ስነ ምግባርን ማዕከል ያደረገ ፍትሐዊና አካታች የሆነ ዘገባ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም