ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በ25 ከተሞች የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጎንደር ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በ25 ከተሞች የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአዲሱ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅና በግማሽ ዓመቱ የአቅድ አፈጻጸም ዙሪያ በጎንደር ከተማ የግምገማ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።፡  

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ካሳ አበባው፤ በክልሉ እስካሁን በባህር ዳር እና ደሴ የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት ስራ መጀመሩን አንስተው በጎንደር ከተማም ለአገልግሎቱ የህንጻ ግንባታ ስራ በመገባደድ ላይ ይገኛል ብለዋል።



 

አገልግሎቱ በተጀመረባቸው ባህር ዳር እና ደሴ ከተሞች ከ14 በላይ የተለያዩ ተቋማት አገልግሎቶች በአንድ ማእከል እየተሰጡ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በቀጣይ በተመረጡ 25 ከተሞች አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችሉ እቅዶች መያዛቸውን አንስተው በተጀመረባቸው ማእከላትም የአገልግሎት አይነቶች እየጨመሩ የሚሄዱ ይሆናል ብለዋል።

ከተሞቹ ሀብት ከማፈላለግ ጀምሮ ለህንጻ ግንባታ የሚውል ቦታ በማዘጋጀትና የዲዛይን ስራዎችን በማከናወን አገልግሎቱን በአጠረ ጊዜ እውን ለማድረግ  በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ገስጥ አሳምናቸው፤ በዞኑ በአይከልና በአምባጊዮርጊስ ከተማ አስተዳደሮች መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የምእራብ ጎንደር ዞን ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ነጋ ከፍአለ፤ በበኩላቸው በገንዳ ውሃ ከተማ አገልግሎቱን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።፡ 


 

ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚካሄደው መድረክ ጎንደር ከተማን ጨምሮ ከማእከላዊ ከሰሜንና ከምእራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ የሲቪል ሰርቪስ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም