ባለፉት ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን ይበልጥ በማጠናከር የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን ይበልጥ በማጠናከር የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ ይሰራል
ጋምቤላ ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን ይበልጥ በማጠናከር እንደ ሀገር የታለመውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ በጋምቤላ ክልል ''ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር'' በሚል መሪ ሃሳብ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመወዳደሪያ ምልክት (የስንዴ ነዶ) እና የማኒፌስቶ የትውውቅ ክልላዊ መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት በምርጫው ለህዝቡ በተገባው ቃል መሰረት በተከናወኑ ተግባራት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ድሎች ተመዝግበዋል።
በቀጣይም የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል እንደ ሀገር የታለመውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በትጋት ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ አሰባሳቢ ትርክቶችን በመገንባትና ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ህዝቡን የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በተለይም በክልሉ ለብዝሃ ኢኮኖሚ ልማት የሚውሉ እምቅ የተፈጥሮ ጸጋዎችን ይበልጥ በማልማት ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ የእድገት ከፍታ እንዲውሉ እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሯ አብራርተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሺኔ አስቲን በበኩላቸው፤ ፓርቲው ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ ስኬቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ፓርቲው በተለይም ሰው ተኮር ለሆኑ የልማት ስራዎች በሰጠው ልዩ ትኩረት በርካታ አቅመ ደካማ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ፓርቲው ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌትና አርዓያ ለማድረግ ተግቶ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።