በምርጫው ተሳትፏችንን በማጠናከር ህገ-መንግስታዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል--አካል ጉዳተኞች - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው ተሳትፏችንን በማጠናከር ህገ-መንግስታዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል--አካል ጉዳተኞች
አምቦ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፏቸውን በማጎልበት ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን በአምቦ ከተማ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ገለጹ።
በአምቦ ከተማ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በምርጫው ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማድረግ ከወዲሁ እየተዘጋጁ ነው።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል መምህር ታሪኩ ተርፋሳ ፤ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በአምቦ ከተማ አካል ጉዳተኞች ማህበር አባላት የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበው በመስራት በከተማና በገጠር የሚገኙ አካል ጉዳተኞች በምርጫው የሚሳተፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
እሳቸውም በምርጫው ለመሳተፍ የመራጮች ምዝገባ ቀንን እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው ምርጫ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚካሄድ በመሆኑ ለአካል ጉዳተኞች አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ብርሃኑ ሞጋሳ ናቸው።
በዚህ ረገድ ከአምቦ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ነፃ ሆኖ እንዲካሄድ ያላቸውን ተሳትፎና ሚና ለመጠቀም አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
የአምቦ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ታርኬ አበራ በበኩላቸው፤ በምርጫው ላይ በመሳተፍ የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎን ለማጠናከር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በጠቅላላ ምርጫው የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ውክልና እንዲሻሻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡም አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።