ለሀገራዊ የምክክር ሂደት ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ የምክክር ሂደት ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ለደረሰው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰለጠነ የምክክር አውድ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት በወሳኝ የምክክር ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ለዚህም በሀገር ውስጥ፤በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ መድረክ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር አሳታፊና አካታችነትም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ ይገኝበታል ተብሎ የሚጠበቅ ስኬታማ ሂደትን እያለፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የፌዴራል ተቋማትና በውጭ ዓለማት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ስኬታማ ምክክር መካሄዱን አስታውሰዋል።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም በአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረኩ በሀገራቸው ጉዳይ አሉኝ የሚሏቸውን አጀንዳዎች በማስረከብ የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረኩም አጀንዳዎችንና ለዋናው ጉባኤ የሚሳተፉ አካላትን በመለየት ማቅረብ መቻላቸውን ተናግረዋል።
በሀገራዊ ምክክር ሂደቱም ፋይዳ ያላቸውና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አጀንዳዎች የመቅረጽ ሥራዎች እየተገባደዱ ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ ተዓማኒና ገለልተኛ የምክክር አመቻች አወያዮች ልየታ መከናወኑን አስረድተዋል።
ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ለደረሰው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬታማነትም ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡