ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ ቃሉን በተግባር በማረጋገጥ ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረገ ነው

ሉሜ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ቃልን በተግባር በማረጋገጥ ህዝቡን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  መስክ ተጠቃሚ  እያደረገ  እንደሚገኝ በፓርቲው የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ገለፁ።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት (የስንዴ ነዶ) እና ማኒፌስቶ የማስተዋወቅ መርሃ ግብር በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ቆቃ ነገዎ ቀበሌ ተካሄዷል።

የፓርቲው የምርጫ ምልክትና ማኒፌስቶ የማስተዋወቅ መርሃግብሩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ፣ በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራና የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማንን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል።

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ከፍያለው በወቅቱ እንደገለፁት፤ ባለፉት ዓመታት ፓርቲው ቃልን በተግባር በማረጋገጥ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ችሏል።


 

ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲው ምልክትና ማኒፌስቶ ስናስተዋውቅ ህዝቡ በሚሰጠን ድምፅ ዳግም ታሪክ ለመስራት ቃላችን በማደስ ጭምር ነው ብለዋል።

ለህዝቡ የገባነውን ቃል ወደ ተጨባጭ ውጤት እየቀየርን ነው ያሉት ሃላፊው፤ ለዚህም ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የኮሪደር ልማት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና ሌሎች ልማቶችን ለአብነት አንስተዋል።

በቀጣዩ አምስት ዓመታትም ትክክለኛ የልማትና ዕድገት ጎዳና ላይ ለማስቀመጥ እንሰራለን ነው ያሉት ።

በዚህም የሀገራችንን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ልማትና ዕድገት አስተማማኝ መሰረት የምንጥልበት ነው ብለዋል።


 

የምርጫ ምልክቱና ማኒፌስቶው የመደመር እሳቤዎች ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅሰው የህዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያ ብልፅግና ራዕይ እውን የሚሆንበት ነው ብለዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆን ፓርቲው የድርሻውን ይወጣል ያሉት አቶ ከፍያለው፤ በምርጫው የህዝብ ድምፅ ለማግኘትና ለማሸነፍ እየሰራን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም