በክልሉ ከ157 ሺህ በላይ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና አጠናቀው የምስክር ወረቀት ወስደዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከ157 ሺህ በላይ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና አጠናቀው የምስክር ወረቀት ወስደዋል
ወራቤ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ157 ሺህ በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና አጠናቀው የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለፀ፡፡
በክልሉ እየተካሔደ ያለውን የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና ኢንሼቲቭ አፈፃፀምን የሚገመግም መድረክ በወራቤ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የእድገትና የትራንፎርሜሽን እቅዶቿን ለማሳካት ካስቀመጠችው አቅጣጫ ውስጥ የዲጂታል ኢትዮጵያ መርሃ ግብር አንዱና ዋነኛው ነው።
በመሆኑም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለፀገች ሀገርን እና በዘርፉ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለመፍጠር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከ218 ሺህ በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን በመውሰድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑት ስልጠናውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ከዚህም 157 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ስልጠናቸውን አጠናቀው የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ዜጎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ በቂ እውቀትና ክህሎት እንዲታጠቁ ከማድረግ በተጨማሪ በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ክልሉ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የተሰጠውን ኮታ ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ሲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል።
በመድረኩም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱን ጨምሮ የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡