የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ስኬት አህጉራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትምህርት የሚቀሰምበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ስኬት አህጉራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትምህርት የሚቀሰምበት ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ስኬት አህጉራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትምህርት የሚቀሰምበት መሆኑን የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት ገለጸ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት ፕሬዝዳንት አሊስ ሩዌዛ፤ ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ውጤት እያስመዘገበች መሆኗን ተናግረዋል።
በተለይም በስንዴና በተለያዩ የሰብል አይነቶች የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶች የግብርና ዘርፍ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ወሳኝ ሚና እንዲወጣ እያስቻሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሰብል ምርታማነትን ለማሻሻል በውሃና የአፈር ለምነት ጥበቃ እንዲሁም በደን ልማት የተከናወኑ ተግባራት አስደናቂ መሆናቸውን አንስተዋል።
ይህም የግብርና ሥርዓትን በማሻሻል ከእርሻ እስከ ጉርሻ ያለውን የእሴት ሰንሰለት ማስተሳሰር ያስቻለ አቅም እንዲፈጠር ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርታማነት ውጤቶች የአፍሪካን ሁለንተናዊ የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ የግብርና ምርቶችን ለገበያ የምታቀርብ አህጉር በመፍጠር ትምህርት የሚቀሰምበት ነው ብለዋል።
የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት የአርሶ አደሮችን የሰብል ምርታማነት አቅም በማሳደግ የግብዓትና የገበያ ትስስር ዕድል ለመፍጠር በትብበር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችና ወጣቶችን ምርታማነት ለማሻሻል የሚደረጉ የድኅረ-ምርት ብክነት ቅነሳና ተያያዥ ተግባራት ላይ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ጥምረቱ የአህጉሪቱን አርሶ አደሮች የግብርና ምርታማነት የሚያሳድጉ ውጤታማ ሙያዊ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።