ቀጥታ፡

የከተማዋን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል እየተገነባ የሚገኘው ፕሮጀክት እየተፋጠነ ነው

ድሬዳዋ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ከተማ ከ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኝ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እየተፋጠነ መሆኑ ተገለፀ ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) በድሬዳዋ ከተማ በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገነባ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃና ማጣሪያ ፕሮጀክት አስጀምረዋል።

በተመሳሳይም በከተማው እየተፋጠነ የሚገኘውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትንም የስራ ሂደት ተመልክተዋል።


 

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የመጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን ችግሮች ለመፍታት አስተዳደሩ ያከናወናቸው ተግባራት የተሻለ አፈጻጸም አላቸው።

ለዚህም የሚደረገው የድጋፍና የክትትል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።

አስተዳደሩ እያከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት፣ የመጠጥ ውሃና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከተማዋን ንፁህና ውብ የመኖሪያና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የታቀደውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ ከከተማው ሁለንተናዊ ዕድገት እና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ከነዋሪው የሚቀርበውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ በጀት ተመድቧል ብለዋል። 

ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው  የመጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክጽ ተጠናቆ ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ  መሆኑን አንስተዋል።              


                                                    

የውሃ ማሰራጫ ቱቦዎችን በመዝጋት ለውሃ ዕጥረትና ብክነት መንስኤ እየሆነ ላለውና ውሃ ውስጥ ለሚገኘው ጨዋማ ንጥረ ነገር አፋጣኝ መፍትሄ ለመፈለግ ጥናቶች መካሔዳቸውን ገልፀዋል።

የጥናቱን ግኝት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጨምሮ የአጋር አካላት እገዛ እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።

የድሬዳዋ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ፤ የከተማውን የመጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል ባለፉት ሶስት አመታት በመገንባት ላይ የሚገኘውን የማስፋፊያ ፕሮጀክት በተያዘው ዓመት መጨረሻ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ  መሆኑን ገልጿል።

የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ  ኢንጂነር መሐመድ ሙሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤  ከ10 በላይ ጥልቅ ጉድጓዶች ፣ የመስመር ዝርጋታና እስከ ግማሽ ሚሊዮን ሌትር ውሃ መያዝ የሚችሉ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች ተገንብተው ተጠናቀዋል።

በቀጣይ ወራት የኤሌክትሮ መካኒካል ቁሶች ግዥና ተከላ በማፋጠን በበጀት አመቱ መጨረሻ ውሃ ለህዝብ ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የከተማው ነዋሪዎች ፕሮጀክቱ ተጠናቆ አገልግሎት የሚጀምርበትን ወቅት በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም