በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን የሚያሻግርና ከፍ የሚያደርግ ሀሳብ እንፈልጋለን -ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን የሚያሻግርና ከፍ የሚያደርግ ሀሳብ እንፈልጋለን -ነዋሪዎች
ሚዛን አማን፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን የሚያሻግርና ከፍ የሚያደርግ ሀሳብ እንደሚጠብቁ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመግለጹ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረገ ነው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች፤ ኢትዮጵያ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መሪዋን በመምረጥ ጠንካራና ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን ለዓለም እንድታሳይ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ብለዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን የሚያሻግርና ከፍ የሚያደርግ ሀሳብ እንጠብቃለን ነው ያሉት።
በክልሉ ሸካ ዞን የቴፒ ከተማ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ ገመዳ ቦንጎሎም፤ መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያደረገው ጥረት የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
የሀሳብ ልዩነትን በማክበር መንቀሳቀስ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ አማራጭ ሀሳብ ከማቅረብ ውጭ የምርጫ ጉዳይን ለሕዝብ መተው ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
በመጪው ጠቅላላ ምርጫም ይበጀኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥም የምርጫ ካርድ የሚወስዱበትን ዕለት እየጠበቁ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ምርጫ፥ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንመራ ትልቅ ሕዝቦች መሆናችንን ለዓለም የምናሳይበት ተጨማሪ ዕድል ይሆናል ያለው ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ዮሐንስ አሊ ነው።
ያለ ምንም ተጽዕኖ የሚመራንን ፓርቲ በነጻነት በመምረጥ የመደማመጥና በሀሳብ የበላይነት የማመን ዴሞክራሲያዊ እሴታችንን ማረጋገጥ አለብን ሲልም ገልጿል።
በቤንች ሸኮ ዞን የሸኮ ወረዳ ነዋሪ የሀገር ሽማግሌ አቶ ካሳሁን ጃርካ በበኩላቸው፤ ምርጫ ሀገረ መንግሥትን የምንገነባበት አንዱ መንገድ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም አለብን ብለዋል።
ከምንም በላይ ሀገር ትቀድማለችና ሀገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል፤ ልማትና ሰላምን የማምጣት ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለይተን በምርጫ መወከል አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
በቅድመ ምርጫ ዝግጅት እና እንቅስቃሴ ወቅት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን የሚያሻግርና ከፍ የሚያደርግ ሀሳብ እንደሚፈልጉ የተናገሩት ደግሞ በዳውሮ ዞን የታርጫ ከተማ ነዋሪ አቶ በለጠ ባልቻ ናቸው።
የከተማዋ ነዋሪ አቶ ፈይሳ ዱባለ በበኩላቸው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም ኮሽታ እንዲካሄድ በየአካባቢው የሰላም ዘብ ሆኖ መቆም ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።