በዞኑ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ ነው
ጭሮ ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ከስደት ተመላሾችን ለመደገፍ ቅንጅታዊ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ገኖ ኢብራሂም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ውስብስብ በሆነ መንገድ የሚፈጸም በመሆኑ ችግሩን ለመከላከል የተቀናጀ እንቅስቃሴን ይጠይቃል።
ዞኑ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መተላለፊያ በመሆኑ ህገወጥ ዝውውሩን የመከላከል ተግባር የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በማሳተፍ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ታዳጊ ህፃናት የችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ለመከላከል ከትምህርት ቤቶች እስከ ዕድር ባሉ ማህበራትና ከተቋማት ጋር ቅንጅት ተፈጥሮ በጋራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በህገወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነት ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል የተማሪዎች ክበባት እንዲቋቋሙ በማድረግ የአቻ ለአቻ ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል።
በየደረጃው ከሚገኙ የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤቶች ጋር በመቀናጀት ወጣቶች በሃገራቸው ሰርተው የሚቀየሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እና ከስደት የሚመለሱ ዜጎችም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል።
በተያዘው ዓመት ብቻ በዞኑ 15 ወረዳዎች ከስደት የተመለሱ 255 ወጣቶች በተደረገላቸው ድጋፍ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራ ዘርፎች መሰማራታቸውን ለአብነት አንስተዋል።
ለእነዚህ ወጣቶች መንግሥት ከ700 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ መሰማራታቸውን አስረድተዋል።
በዞኑ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት የሴቶችና ህፃናት ወንጀል ስራ ሂደት መሪ ወይዘሮ በድሪያ መሐመድ በበኩላቸው፤ በዞኑ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በአዘዋዋሪዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት 12 አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ ተደርጎ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው እያንዳንዳቸው ከ3 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ መደረጉን ገልፀዋል።
የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈባቸው መካከል ወጣቶችን በተደጋጋሚ በማታለል ድንበር እንዲያቋርጡ ከማድረግ ባለፈ እገታ በመፈፀም ወደ ቤተሰቦቻቸው በማስደወል ገንዘብ ሲጠይቅ የነበረ ግለሰብ በ15 ዓመት ጽኑ እስራትና የ20 ሺህ ብር ቅጣት እንደተላለፈበትም አክለዋል።
በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህር ጀማል አህመድ፤የተሳሳተ ግንዛቤና ያልተገባ ተስፋ መያዝ በዋናነት ወጣቶችን ለስደት እንደሚዳርግ ተናግረዋል።
አብዛኞቹ ወጣቶች ለህገወጥ አዘዋዋሪዎች እስከ 200 ሺህ ብር እንደሚከፍሉ ገልፀው ገንዘቡ በሃገር ውስጥ ስራ ፈጥረው ቢሰሩ የተሻለ ህይወት ሊመሩ እንደሚችሉም አስረድተዋል።
ወጣቶች በሃገር ሰርቶ ለመለወጥ ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ ጠቅሰው ለዚህም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያልተቆጠበ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።