የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ልማት ውጤታማነት አፍሪካን ከተጠቃሚነት ወደ አምራችነት የሚያሸጋግር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ልማት ውጤታማነት አፍሪካን ከተጠቃሚነት ወደ አምራችነት የሚያሸጋግር ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ልማት ውጤታማነት አፍሪካን ከተጠቃሚነት ወደ አምራችነት የሚያሸጋግር መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ገለጸ።
በተመድ የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ረዳት አስተዳዳሪና የአፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ-ኦኖቺ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና ኢኮኖሚ ልማት አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ነው።
የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን የኢኮኖሚ ልማትም አፍሪካን ለቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተመዘገበው ፈጣን የዲጂታላይዜሽን ሽግግርም የአፍሪካ ሀገራት የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን መስበር እንደሚችሉ ትምህርት የሰጠ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለዲጂታል ልማት የወሰደው ቁርጠኛ አቋም አህጉሪቷ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በሳይንስ መስክ ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።
ለሀገር በቀል የምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት የተሰጠው ትኩረትም የዲጂታል ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
በተለይም የዜጎችን የመልካም አስተዳደርና የመንግስት አገልግሎቶች ፍላጎት አፋጣኝ ምላሽ በማስገኘት ብልሹ አሰራርና ሙስናን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ አስደናቂ ዲጂታላይዜሽን ሽግግር ለማፋጠን አስፈጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነትም ለዜጎች ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎቶችን በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
የዲጂታል አገልግሎቶችም ብልሹ አሰራርን በማስወገድ ተዓማኒ የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ሥርዓትን በማስፈን ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም በልማት አጋሮች አድናቆት የተቸረውና የሀገሪቱን ዕድገት በማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።