ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ አርሰናል ከዎልቭስ ጋር ይጫወታል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018 (ኢዜአ)፡- ዎልቨርሃምፕተን ዎንድረርስ ከአርሰናል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ31ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን  ዛሬ ያደርጋሉ። 

ጨዋታው ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በሞልኒው ስታዲየም ይካሄዳል።

ዎልቭስ በዘጠኝ ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል። አርሰናል በ57 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 26 ጨዋታዎች መካከል አንዱን ብቻ ያሸነፈው ዎልቭስ 19 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 16 ግቦችን ሲያስቆጥር 48 ጎሎችን አስተናግዷል።

ተጋጣሚው አርሰናል በበኩሉ 26 ጨዋታዎችን አድርጎ በ17ቱ ድል ሲቀናው ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። ስድስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 50 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ 18 ጎሎች ገብተውበታል።

ዎልቭስ በሊጉ ሁለተኛ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።  


 

መርሐ-ግብሩ አርሰናል በ26ኛ ሳምንት ከብሬንትፎርድ ጋር አቻ ከወጣበት ጨዋታ በኋላ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርገው ነው።

መድፈኞቹ ካሸነፉ ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ ሰባት ከፍ ያደርጋሉ። 

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር በኤምሬትስ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ አርሰናል 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች የ31ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ሊያደርጉ የነበረው በመጋቢት ወር 2018 ዓ.ም ነበር። 

ይሁንና አርሰናል በካራባኦ ፍጻሜ ከማንችስተር ሲቲ ጋር ጨዋታ የሚያደርግበት ወቅት ከ31ኛው ሳምንት መርሐ-ግብር ጋር በመጋጨቱ ምክንያት ጨዋታው ላይ ማስተካካያ ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም