ቀጥታ፡

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ የሁለተኛ ቀን ውሎ 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018 (ኢዜአ)፦  በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ምሽት አምስት ላይ ቦዶ ግሊምት ከኢንተር ሚላን በአስፕማይራ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የኖርዌው ቦዶ ግሊምት በሊግ እርከን የውድድር ምዕራፍ በዘጠኝ ነጥብ 23ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።

ኢንተር ሚላን በ15 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ሁለቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። 

እ.አ.አ በ1978/19 በአውሮፓ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ተገናኝተው ኢንተር ሚላን በደርሶ መልስ የተደረጉትን ጨዋታዎች 5 ለ 0 እና 2 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል።

በሌላኛው መርሐ-ግብር ክለብ ብሩዥ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ምሽት አምስት ሰዓት በጃን ብሬይዴል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በሻምፒዮንስ ሊጉ የሊግ ውድድር ምዕራፍ ክለብ ብሩዥ በ10 ነጥብ 19ኛ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ በ13 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲገናኙ ለአምስተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ አንድ ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ካራባግ ከኒውካስትል ዩናይትድ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በቶፊቅ ባህራሞቭ ስታዲየም ይጫወታሉ።


 

የአዘርባጃኑ ካራባግ በሊግ ምዕራፉ በ10 ነጥብ 22ኛ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ በ14 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዘው መጨረሳቸው ይታወቃል።

ሁለቱ ቡድኖች በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ጋላታሳራይ ከጁቬንቱስ በራምስ ፓርክ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

በውድድሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጋላታሳራይ በ10 ነጥብ 20ኛ፤ ጁቬንቱስ በ13 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

ከዚህ ቀደም በሻምፒዮንስ ሊጉ በነበራቸው አራት ግንኙነቶች ጋላታሳራይ ሁለት ጊዜ አሸንፏል። ጁቬንቱስ በአንዱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የክለቦቹ የመልስ ጨዋታዎች በቀጣዩ ሳምንት ይደረጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም