የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወሳኝ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወሳኝ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ አምጥቷል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ንግድና ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዝዳንት አድማሱ ታደሰ ገለፁ።
የኢትዮጵያ የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን፣ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ እና የፊስካል ማሻሻያዎችን በመተግበር ጠንካራ፣ አካታችና ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለመ ነው።
የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ንግድና ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዝዳንት አድማሱ ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት መንግስት የወሰደው የኢኮኖሚ ሪፎርም እርምጃ የሚደነቅና የሀገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ መነቃቃት ለአፍሪካ የፋይናንስ ትስስር ቅንጅት ወሳኝ መሆኑንም ነው ጨምረው የተናገሩት።
የፋይናንስ ዘርፉ ክፍት መሆንና የፖሊሲ ማዕቀፎች መሻሻል፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ከአህጉራዊ አጋሮቻቸው ጋር ያላቸውን ትብብር በማጠናከር ለዘላቂ ብልጽግና በጋራ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ማሻሻያው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል የጎላ ሚና እንዳለውም አክለዋል።
አሁን ላይ የኢትዮጵያን ባንኮች ጨምሮ በአፍሪካ ያሉ ባንኮች አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ይህን የበለጠ በማጠናከር አህጉሪቱ የራሷን ትልቅ ተቋም መገንባት አለበት ብለዋል።
በአፍሪካ ያሉ ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት በቅንጅት በመስራት ለአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አሁን ላይ በአህጉሪቱ ያላቸው አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ይህን አቅም ለአህጉሪቱ እድገት እና ዘላቂ ብልጽግና ለማፋጠን በትብብር ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ባንኮች አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፣ ለአብነትም የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ንግድና ልማት ባንክ ካፒታል ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱን ጠቁመዋል።