ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ የአቪዬሽን ደኅንነትን የመፈፀም አቅም የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኩዩሪቲ ረቂቅ አዋጅ የአቪዬሽን ደኅንነትን የመፈፀም አቅም የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኩዩሪቲ አዋጅ ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በዚህ ወቅት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሕግ ዳይሬክተር አማረ ኢቲቻ እንደገለጹት፤ ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ የሽብርተኝነትና የተደራጁ ወንጀሎች አፈፃፀም እየተወሳሰበ መጥቷል።

የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፉን በላቀ ሁኔታ ለመከላከል ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር የተጣጣመ ህግ ማውጣት በማስፈለጉ አዋጁን ማሻሻል ማስፈለጉን አንስተዋል።


 

እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 432/1997 ሃላፊነት የተሰጣቸው ባለድርሻ አካላት የስያሜ ለውጥ በማድረጋቸው ለአዋጁ መሻሻል ምክንያት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በውይይት የተገኙና የአቪዬሽን ዘርፉ ባለድርሻ አካላት የአቪዬሽን ደህንነት አዋጅ ቁጥር 432/1997 ለማሻሻል መነሻ የሆኑ ምክንያቶችንና የባለድርሻ አካላትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ሰጥተዋል።

የተሻሻለው አዋጅ ለአቪዬሽን ዘርፉ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ የሚበረታታ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኩዩሪቲ አዋጅ ማሻሻል ለዘርፉ እድገት እና ደህንነት መጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ነው የተጠቀሱት።


 

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሲሳይ ቶላ  በሰጡት ማብራሪያ፤ ረቂቅ አዋጁ በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መስፈርት መሰረት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ መህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ የአቪዬሽን ደኅንነት አስተማማኝነትን በማጠናከር የዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ተቀባይነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።


 

ረቂቅ አዋጁ የአቪዬሽን ዘርፉን ከተለያየ የሽብር ጥቃት ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን የበለጠ የሚያጠናክርና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን አንስተዋል።

የአዋጁ መሻሻል የዜጎችን ደህንነት በማረጋገጥ የሃገርን እድገትና ብልፅግና እውን በማድረግ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያመጣና አሰራርን ለማዘመን ያስችላል ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁ ሲጸድቅ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል በጥራቱና ቅልጥፍናው የአቪዬሽን ደህንነትን ለማጠናከር የሚያስችል እንዲሁም የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራርን የሚያበረታታ እንደሚሆን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም