ቀጥታ፡

ቱርክዬ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር ትሻለች-  ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10 /2018(ኢዜአ):- ቱርክዬ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ትብብር የበለጠ ለማጎልበት ቁርጠኛ መሆኗን የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር ከተወያዩ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን በወቅቱ ቱርክዬ እና ኢትዮጵያ ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ቱርክዬ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት የረጅም ጊዜ ትብብር ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥ እና አጋርነቷን ማጠናከር እንደምትሻም ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ መሰረተ ልማት፣ ባህል፣ ትምህርት እና ሌሎች መስኮች የሁለትዮሽ ትስስሩን ለማጎልበት ቁርጠኛ ናት ብለዋል።

ቱርክዬ ከኢትዮጵያ ጋር በእኩል አጋርነት እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተውን ግንኙነቷን እንደምታጠናክር ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት።

በሌላ በኩል የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስልጣን ከያዙ ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ያከናወኑትን ስራ አድንቀዋል።

ዓለም ፊቱን ወደ አፍሪካ ቀንድ ባዞረበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ጸንቶ የቆየ የሀገረ መንግስት መዋቅር እና ተምሳሌታዊ አስተዳደር የበለጠ አስፈላጊ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ችግሮች ያለ ምንም ውጫዊ ጣልቃ ገብነት በቀጣናው ሀገራት ብቻ ሊፈታ እንደሚገባ እና ቀጣናው የጂኦ ፖለቲካ መፎካከሪያ መድረክ መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል።

የአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ እድሎች ያሉበት ቀጣና እንደሆነም ተናግረዋል።

የዛሬው ጉብኝት መልካም ውጤቶች ይዞ እንደሚመጣ እና ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለእሳቸው እና ለልዑካቸው ላደረጉት ደማቅ አቀባበል ፕሬዝዳንቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም