በክልሉ ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ ነው
ወልቂጤ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለስፖርት ልማት ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ብቁ፣ በስነምግባር የታነጹና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
3ኛው ዙር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ ልዩ ሻምፒዮና፣ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ማስጀመሪያ መርሐግብር በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ተጀምሯል።
የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሶ እንዳሉት፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የስፖርት ልማትን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ ብቁ፣ በስነምግባር የታነጹና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ ነው።
ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት በወልቂጤ ከተማ የሚካሄደው 3ኛው ዙር የልዩ ልዩ ስፖርት ሻምፒዮናና የባህል ስፖርት ውድድርም በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የክልሉን ገጽታ ለመገንባት ካለው ፋይዳ በተጨማሪ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ያጠናክራል ብለዋል።
ውድድሩ በ17 የስፖርት አይነቶች እንደሚካሄድ ጠቁመው፣ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በስፖርታዊ ጨዋነት፣ በወዳጅነት፣ በመቻቻልና በመከባበር መሳተፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ስፖርታዊ ውድድሮች የክልሉን ማህበረሰብ አንድነትና የእርስ በርስ ግንኙነት ያጠናክራሉ ያሉት ድግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ንጉሴ አስረስ (ዶ/ር) ናቸው።
ስፖርት ህብረ ብሔራዊ አንድነትና አብሮነትን በማጎልበት ሀገራዊ የጋራ ትርክትን ለመገንባት ሚናው የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ በስፖርት ልማት ወጣቱን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የስፖርት መሰረተ ልማት የማሟላት ሥራ መከናወኑን ገልጸው፣ በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል ብለዋል።
ስፖርታዊ ውድድሮች በተለይ የወጣቶችን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ያሉት ደግሞ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ናቸው።
ስፖርት ጤንነቱ የተጠበቀና በስነ ምግባር የታነጸ አምራች ዜጋ ለመፍጠር ጉልህ ሚና ስላለው ዞኑ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።