ቀጥታ፡

በተደመረ አቅም ህዝብ ተኮር የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- ርእሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ወላይታ ሶዶ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡- በክልሉ ያሉ እምቅ አቅሞችን በመጠቀም በተደመረ አቅም ህዝብ ተኮር የልማት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ ምልክት(የስንዴ ነዶ) እና ማኒፌስቶ ይፋ ማድረጊያ ክልላዊ መርሃ ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን  ከበደ፤ ፓርቲው በስድተኛው ጠቅላላ ምርጫ  ለህዝቡ የገባውን ቃል መነሻ አድርጎ በመስራት በርካታ ፈተናዎችን በድል ተሻግሮ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ደርሷል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የመደመር ጉዞ ወደ አዲስ የማንሰራሪያ ምዕራፍ በማሻገር በክልሉ በሁሉም ዘርፎች ስር ነቀል ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉንም ተናግረዋል።


 

በፓርቲው መሪነት ሀገርን ከብተና ህዝብን ከመከራ የታደጉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የክልሉን ህዝብ የመልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በቆራጥነት ምላሽ በመስጠት የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ክልል ለማድረግ የተጀመረው ውጥን እንደሚጠናከርም ገልጸዋል።

ባለፉት የለውጥ  ዓመታት በብልጽግና ፓርቲ አዲስ ዕሳቤ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያንን ያሳተፉ የልማት ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን የገለጹት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ናቸው።


 

ፓርቲው የሃሳብ ልዩነት ወደ ጋራ መግባባት እንዲመጣ በር በመክፈት አካታችነትን በተግባር ማረጋገጥ መቻሉንም ጠቁመዋል።

የክልሉን የመልማት አቅም በመለየት  በግብርና ፣በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝምና በሌሎችም የኢኮኖሚ ዘርፎች የመጣውን መነቃቃት ለማስቀጠልና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መሰራቱ ውጤት ለማምጣት ማስቻሉንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ጤናማ ውድድር በማድረግና ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ የህዝቡን የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ለማሳለጥ እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም