ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ የንግድ ልውውጣቸውን ለማሳደግ ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ የንግድ ልውውጣቸውን ለማሳደግ ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እና በቱርኪዬ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ ስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዝዳንት ረጀብ ጣይፕ ኤርዶዋን በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
መሪዎቹ የሁለትዮሽ ውይይታቸውን በማስመልከትም የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመግለጫቸው በአንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ከቱርክዬ ፕሬዚዳንት ጋር ተግባብተናል ብለዋል።
በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ እና ከዛም በላይ እንዲያድግ በሁለቱም መንግስታት በኩል ታቅዶ እንዲሰራበት ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
በተለይም የቱርክዬ ሁነኛ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት በማድረግ ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ገበያ ኤክስፖርት ማድረግ እንዲችሉ በትብብር እንድንሰራ ተጨማሪ ኢንቨስተሮች እንድናመጣ ተነጋግረናል ሲሉም አስታውቀዋል።
በ9ኛው የቱርክ-ኢትዮጵያ የጋራ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ስምምነት ሰነድ እንዲሁም በኢነርጂ ዘርፍ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድም ተፈራርመዋል።
ስምምነቶቹ በኢትዮጵያ እና በቱርክዬ መካከል እየተጠናከረ የመጣውን አጋርነት ይበልጥ የሚያጎለብቱና፤ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረቱ መስኮች፤ ያላቸውን የሥራ ግንኙነት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ያመላከቱበት እንደሆነም ተመላክቷል።