ኢትዮጵያና ቱርክዬ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ቱርክዬ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና ቱርክዬ የንግድ ልውውጥን ጨምሮ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጠይብ ኤርዶዋን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ከውይይታቸው በኋላም የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በወቅቱ ከቱርክዬ ፕሬዝዳንት ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች መደረጉን ነው ያመለከቱት።
እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን በዘጠነኛው የቱርክ-ኢትዮጵያ የጋራ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ስምምነት ሰነድ እንዲሁም በኢነርጂ ዘርፍ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ስምምነቶቹ በኢትዮጵያ እና በቱርክዬ መካከል እየተጠናከረ የመጣውን አጋርነት ይበልጥ የሚያጎለብቱ ሲሆን፤ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረቱ መስኮች፤ ያላቸውን የሥራ ግንኙነት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አመላካች መሆኑም ተገልጿል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ጠቁመው፤ የቢዝነስ ዘርፎችም እንዲሰፉ ስምምነት ላይ መደረሱን ነው ያብራሩት።
በተጨማሪም የቱርክዬ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያሳድጉ መጠየቁን ጠቁመው፤ ከሀገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ ለአፍሪካ ሀገራት ወጪ ንግድ ማድረግ በሚችሉበት ዙሪያ መስማማታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ቱርክዬ በአውሮፓና በአፍሪካ መካከል ያላትን የኢኮኖሚ ሚና በመጠቀም ለቀጣናዊ ዕድገት እንድትሰራ ስምምነት ላይ መደረሱንም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የመልካ ምድር እስረኛ ሆና መቆየቷን ገልጸው፤ ይህንን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የቱርክዬ መንግስት ዲፕሎማሲያዊ ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል።
በፀጥታው ዘርፍ ሁለቱ ሀገራት በጸረ-ሽብር ትግሉ በጋራ ለመስራት ቃላቸውን ማደሳቸውን አስታውቀዋል።
በተያያዘም ኢትዮጵያ ለምታዘጋጀው በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP) ላይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ተስማምተዋል።