በአማራ ክልል ሰላምን በማጽናት የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሰላምን በማጽናት የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
ባህርዳር ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ሰላምን በማጽናት በከተሞችና በገጠር የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል መሐመድ ተሰማ እና የአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በባህር ዳር ከተማ የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ሰላምን በማጽናት በከተሞችና በገጠር የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
በከተሞች የኮሪደር ልማትን እና የአገልግሎት አሰጣጡን የሚያዘምኑ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎችም የዲጅታል አገልግሎቶች በመስፋፋት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በገጠርም የአርሶ አደሩን አኗኗር የሚያሻሽሉ እንዲሁም የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው የቀጠሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ፤ ባህር ዳር ከተማ ያሏትን የተፈጥሮ ፀጋ የበለጠ አጉልተው የሚያሳዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው ከተማዋን ለጎብኝዎችና ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በከተማዋ በሶስተኛው ዙር የኮሪደር ልማት የመኪና፣ የእግረኞችና የብስክሌት መንገዶችን ጨምሮ መዝናኛዎችና ሌሎችም የልማት ሰራዎች በጥራትና በፍጥነት እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ በጣና ዳርቻ የተካሔዱ የልማት ስራዎች የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ማስቻሉን አብራርተዋል።
አሁንም የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ከማድረግ ጎን ለጎን የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ማህበረሰቡን በማሳተፍ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በዛሬው የመከላከያ፤ የክልሉና ከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጉብኝት በጣና ማሪና፣ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የኮሪደር ልማት፣ የባህር ዳር ስታድየም እና ሌሎችም አካባቢዎችን ያካለለ ነበር።