ቀጥታ፡

የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለፍጻሜ እንዲበቁ  ተሳትፏችንን እናጠናክራለን -ወጣቶች

ጎንደር ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡- የአካባቢያቸውን  ሠላም በማጽናት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለፍጻሜ እንዲበቁ ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ  የጎንደር ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

"የወጣቶች መሪነት ለዘላቂ ሠላም" በሚል መሪ ሀሳብ የከተማው ወጣቶች የተሳተፋበት የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።  

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ሳሙኤል አየለ፤ የኢትዮጵያ ፈጣን እድገትና የወደፊት የልማት ግስጋሴ ያስፈራቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሸረቡትን ሴራ በማክሸፍ በኩል ወጣቶች ዝግጁ ነን ሲል ገልጿል።

በአካባቢያችን ለወጣቱ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው ያለው ወጣት ሳሙኤል ግጭት ልማት አደናቃፊ በመሆኑ ወጣቱ ለሰላም አጥብቆ ይሰራል ብሏል፡፡

የአካባቢያችንን ሠላም በማጽናት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለፍጻሜ እንዲበቁ  ተሳትፏችንን እናጠናክራለን ሲልም አመልክቷል።


 

መንግስት የወጣቱን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የጀመራቸው ስትራቴጂክ እቅዶች ሰላምን አጥብቀው የሚሹ ናቸው ያለው ደግሞ ወጣት ጅብሪል መሃመድ ነው፡፡ 

ወጣቱ ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡ 

ወጣት ማሩ መንገሻ በበኩሉ፤ የወጣቱ የነገ ተስፋና ምኞቱ ሀገር በልጽጋና አድጋ በሀገሩ ሰርቶ መለወጥ በመሆኑ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የድርሻችንን ለማበርከት ዝግጁ ነን ብሏል፡፡

የኢትዮጵያን ሠላም ለማደፍረስና ልማቷን ለማደናቀፍ የሚሯሯጡ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን  የጥፋት ተልእኮ ለመመከት ዝግጁ ነን ሲልም አክሏል።


 

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዘላለም ይርጋ በበኩላቸው፤ ለክልሉ ለሰላም መረጋገጥና ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ በኩል የወጣቱ ሚና ከፍተኛ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ በበኩላቸው፤ ወጣቱ አንድነቱን በማጠናከር የአካባቢውን ሰላም ተደራጅቶ ከመጠበቅ ጎን ለጎን  የከተማው የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

በውይይት መድረኩ ላይ ወጣቶችን ጨምሮ የክልሉ፣ ማእከላዊ ጎንደርና የጎንደር ከተማ አስተዳደር አመራሮች የተገኙ ሲሆን "የወጣቶች የሰላም አበርክቶ" በሚል በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም