የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆ በመፍታት ለዘርፉ ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆ በመፍታት ለዘርፉ ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ማስቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
የ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤክስፖ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ መፋጠን የአምራች ኢንዱስትሪውን አቅም ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መጀመሩን አውስተዋል።
ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ማስቻሉን አንስተዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፋ አጠቃላይ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ያለው ድርሻ በየጊዜው እያደገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንዲሁም ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር ዘርፉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እና የንግድ ሚዛንም እንዲስተካከል ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከሚያዝያ 24–28/2018 ዓ.ም ድረስ ከ270 በላይ አምራቾች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል።እንዲሁም ከ50 በላይ የጎንዮሽ ሁነቶች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።
ከሀገር ውስጥና ከውጭ በርካታ የንግድ ስምምነቶችና የገበያ ትስስሮች ይፈጠራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
መንግስት በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሕግ ማዕቀፎችን ከማሻሻል ባለፈ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል የዘርፉን ችግሮች በየደረጃው በመፍታት እና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
በፍጥነት እና ፈጠራ በተሞላበት አግባብ በመስራት መስፈንጠር እንደሚገባ በማንሳት፥ በኤክስፖው የሚሳተፉ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ጥራት ላይ ከወዲሁ መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፍቃዱ መንግስቱ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ የመገናኛ ብዙኃን የስራ ኃላፊዎች፣ የአጋር አካላት ተወካዮች፣ ባለሃብቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።