ቀጥታ፡

ብቃት ያለው የሰው ሀይል በጥራት እና በብዛት ለማፍራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡-ሀገር የሚያሻግር ብቃት ያለው የሰው ሀይል በጥራት እና በብዛት ለማፍራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተደርጓል ሲሉ  የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

የመንግስት አገልግሎት ፈጠራ ማሻሻያ ማዕከል አካል የሆነው ማለዳ የውይይት መርሃ ግብር "ቴክኒክና ሙያ ዩኒቨርሲቲ እና ኢንተርፕርነርሺፕ" በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።

በውይይት መርሃ ግብሩ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።


 

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት፤ ማለዳ የውይይት መርሃ ግብር ከተጀመረ አንድ ዓመት እንደሆነው ጠቁመው፤ ዋና ዓላማውም የሀገሪቱን የሰው ኃይል ልማት ከገበያው ፍላጎት ጋር ለማጣጣም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ያለውን የሰው ኃይል ልማት ውጤታማ ለማድረግ ገበያ መር የሆነ የክህሎት ስልጠና ስርዓት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን አመላክተዋል፡፡

አሁን ላይ ስልጠናዎች በቀጥታ ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣሙ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ሥራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪ እየሆኑ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ይህም በኢንዱስትሪው ውስጥ ይታይ የነበረውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ትርጉም ባለው መልኩ ማቃለሉን አመላክተዋል፡፡

በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሀገር የሚያሻግር ብቃት ያለውና ክህሎት መር የሰው ሀይል በጥራት እና በብዛት ለማፍራት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የተናገሩት፡፡


 

ከትምህርት ሚኒስቴር የመጡት መሰረት ደርቤ በበኩላቸው፤ ትምህርት ሚኒስቴር ገበያ መር የክህሎት ልማትን እውን ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ለዘርፉ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ አዋጆች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን አመላክተዋል፡፡

የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሐሰን ሑሴን (ዶ/ር)፤ ዜጎች ክህሎታቸውን አዳብረው ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ስልጠና መስጠት ከኢንስቲትዩቱ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡


 

በመሆኑም ችግር ፈች የሆነ የሰው ሃይል ለማፍራት በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በበኩላቸው፤  አካዳሚያቸው ለገበያ መር የሰው ሃይል ግንባታ ውጤታማነት የራሱን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡


 

ተማሪዎች የንድፈ ሃሳብ ትምህርታቸውን ወደ ተግባር የሚተረጉሙበት ልዩ ልዩ ላብራቶሪዎች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም