የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስገኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስገኝተዋል
ጎንደር ፤የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡- የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገባቸው ተመለከተ።
"በሴቶች ተሳትፎ የጸናችና የበለጸገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ያዘጋጀው መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ሃላፊ ወይዘሮ እሌኒ አባይ እንደተናገሩት፤ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ፖሊሲዎች፣ አዋጆችና መመሪያዎች ስራ ላይ እንዲውሉ በመደረጉ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡
መንግስት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም የሚገነቡ ሰፋፊ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቁመው በለውጡ አመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች ሁሉ ሴቶችን ማእከል ያደረጉ እንደነበሩ አውስተዋል፡፡
የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻርም ሴቶች እራሳቸውን በማደራጀት በሀገረ መንግስት ግንባታው የላቀ ሚናና ተሳትፎ እንዲኖራቸው ምቹ የፖለቲካ አውድ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡
የክልሉ ሴቶች ከልማት ተሳትፏቸው ባሻገር በሰላም ግንባታ ተግባራት ዙሪያ የክልሉ ሰላም ጸንቶ እንዲቀጥል ሁለገብ አበርክቷቸው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን ልማትና እድገት የማይሹ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በውስጥ ተላላኪዎቻቸው አማካኝነት የሚፈጽሙትን ግጭት በማክሸፍ በኩል ሴቶች ዛሬም እንደ ትናንቱ ታሪካዊ ተጋድሏቸውን ሊደግሙ ይገባል ብለዋል፡፡
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በተግባር የሚያረጋግጡበት የሃሳብ ልእልና መገለጫ በመሆኑ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የምርጫ ተሳትፎ ማድረግ አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ በጉልህ በተጻፈ የታሪክ አሻራ ተቀምጧል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ናቸው፡፡
የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ሴቶች በመጪው ምርጫ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሀገር የማስቀጠል ታሪካዊ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡
በመድረኩ የክልሉ፣ የማእከላዊ ጎንደር ዞንና የጎንደር ከተማ አመራሮችን ጨምሮ ሴት የመንግስት ሰራተኞችና የሴት አደረጃጀት አባላት እየተሳተፉ ነው።