ብልጽግና ፓርቲ ሁሉም በባለቤትነት የሚሳተፍባትና ተጠቃሚ የሚሆንባት ሀገር በመገንባት ምሳሌ የሆነ ሥራ ሰርቷል--ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ ሁሉም በባለቤትነት የሚሳተፍባትና ተጠቃሚ የሚሆንባት ሀገር በመገንባት ምሳሌ የሆነ ሥራ ሰርቷል--ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፤የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡-ብልጽግና ፓርቲ ሁሉም በባለቤትነት የሚሳተፍባትና ተጠቃሚ የሚሆንባት ሀገር በመገንባት ምሳሌ የሆነ ሥራ መስራቱን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ፓርቲው አግላይ የፖለቲካ እሳቤን በማስወገድ በክልሉ ለተመዘገበው ተጨባጭ ልማትና መነቃቃት ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የምርጫ መወዳዳሪያ ምልክቱ የሆነውን የስንዴ ነዶ እና ማኒፌስቶ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተዋውቋል።
የክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ፓርቲው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶችን በመጠገን እና የህዝብን ጥያቄዎች በመመለስ ተጨባጭ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ፓርቲው ወደስልጣን በመጣበት ወቅት የህዝቦች አብሮነትን የሚሸረሽሩ በርካታ ችግሮች ሀገርን ሲፈትኑ እንደነበር አስታውሰው፣ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ በማበጀትና አሰራር በመዘርጋት ዛሬ ላይ ለሌሎች ምሳሌት የሆነች ሀገር መፍጠር ችሏል ብለዋል።
ፓርቲው አቃፊ በሆነ መልኩ የህዝቦችን ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ አግላይ የነበረውን አተያይ መቀየር ችሏል ያሉት አቶ ደስታ፣ ሁሉም በባለቤትነት የሚሳተፍባትና ተጠቃሚ የሚሆንባት ሀገር በማስቀጠል ምሳሌ የሆነ ሥራ መስራቱንም ጠቅሰዋል።
ሲዳማም በአግላይ የፖለቲካ አተያይ ሳቢያ በብዙ ሲቸገር እንደነበር አንስተው፣ በፓርቲው መሪነት በክልሉ የህዝብን የልማትና መልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተጨባጭ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ፓርቲው በየአካባቢው ያሉ የልማት ፀጋዎችን ለይቶ አውጥቶ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም በማዋል በኩል አስደማሚ ተግባራት እያከናወነ ያለ ፓርቲ መሆኑንም አቶ ደስታ አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከማጠናቀቅ ባለፈ ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመጀመር ኢትዮጵያን የብልጽግና ማማ ላይ ለማድረስ እየተጋ ያለ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርቲው የሀገርን መጻኢ ዕድል ተልሞ በመስራት አስደማሚ የልማት ስኬቶችን እያስመዘገበመሆኑን ጠቅሰው፣ ዜጎች በቀጣይ ምርጫ ብልጽግናን በመምረጥ እነዚህን የልማት ስኬቶችና ተጠቃሚነታቸውን አጠናክሮ ማስቀጠል መሆኑን ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በበኩላቸው ፓርቲው በሚከተለው የመደመር ዕሳቤ ትናትን በማከምና ነገን በመተለም አኩሪ ሥራዎች እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።
በዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲውን መምረጥ በልማትና በመልካም አስተዳደር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የምርጫ መወዳዳሪያ ምልክቱ የሆነውን የስንዴ ነዶ እና ማኒፌስቶ ለማስተዋወቅ በሃዋሳ ከተማ ባዘጋጀው መድረክ የክልሉ መንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል።