ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለነበሩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ወሳኝ ሚና አለው-አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች

አዳማ፤  የካቲት 10/2018 (ኢዜአ) ፡-ሀገራዊ ምክክሩ ለነበሩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን ሲሉ የኦሮሞ አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ገለፁ።

ለኢዜአ አስተያየት ከሰጡት መካከል የቱለማ ኦሮሞ አባ ገዳና የህብረቱ ፀሓፊ ጎበና ሆላ እንደገለፁት በኦሮሚያ ክልል በተካሄደው የምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በሀገራችን ዘላቂ መፍትሄ ያላገኙ አለመግባባቶችና ግጭቶችን በውይይትና በምክክር ለመፍታት ይረዳል ብለን ያመንበትን አጀንዳ ሰጥተናል።

ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮቻችንን በዘላቂነት ለመፍታት የማይተካ ሚና ያለውና የመፍትሔ ሃሳብ የሚገኝበት ነው ብለዋል።

የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የህዝብ ተወካዮችን ጨምሮ የሀገር ጉዳይ ያገባኛል የሚል አካል በሙሉ ከሂደቱ ጀምሮ እየተሳተፈበት መሆኑን ጠቅሰው ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ አሁንም የሚጠበቅብንን ድርሻ እንወጣለን ነው ያሉት።

የምክክር ውጤቱ የህዝብ ፍላጎትና ውሳኔ የሚፀናበት በመሆኑ ምክክሩ ግቡን እንዲመታ መደገፍ እንደሚገባ አባገዳው አስገንዝበዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የመጫ ኦሮሞ አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ በበኩላቸው የምክክር ሂደቱ ሁሉንም የህብረሰተብ ክፍሎችን ከታችኛው ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የፖለቲካ ልህቃን ድረስ ያሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክክሩ  ችግሮቻችንን በዘላቂነት ከመፍታት ባለፈ የሀገሪቷን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ  ልማትና እድገት እንዲፋጠን ወሳኝ ሚና አለው ነው ያሉት።

በዚህም በህዝቦች መካከል መተማመን፣ አንድነት፣ አብሮነትና ፍቅርን በማጽናት ሀገራችንን ወደ ታሰበው የእድገትና ብልፅግና ጎዳና ለመውሰድ ሚናው የማይተካ መሆኑን ገልጸዋል።

በምክክሩ ሂደት የነበረን ተሳትፎ በማጠናክር ዋናው ምክክሩ እንዲሳካ የድርሻችን እንወጣለን ያሉት አባገዳ ወርቅነህ በምክክሩ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ጭምር ወደ መሬት ለማውረድ እንሰራለን  ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሂዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባት የሆኑት መጋቢ ሃዲስ ቀሲስ ለማ በየነ እንደገለፁት የነበሩብንን ችግሮች፣ አለመግባባቶችና ግጭቶችን ለማስወገድ ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ነው ብለዋል። 

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉት የሀገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ አካላት በሙሉ በምክክር ሂደቱ እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ በማጠናከር ምክክሩ እንዲሳካ ማድረግ አለብን ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም