በካፒታል ገበያ የሚነሱ ክርክሮችን በብቃት ለመዳኘት የሚያስችል መጽሐፍ ለዳኞችና ለሕግ ባለሙያዎች ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
በካፒታል ገበያ የሚነሱ ክርክሮችን በብቃት ለመዳኘት የሚያስችል መጽሐፍ ለዳኞችና ለሕግ ባለሙያዎች ተዘጋጀ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡-በካፒታል ገበያ የሚነሱ ክርክሮችን በብቃት ለመዳኘት የሚያስችል የመመሪያ መጽሐፍ (Guide Book) ለዳኞችና ለሕግ ባለሙያዎች ተዘጋጀ።
በመፅሐፉ ዙሪያ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ አብነት ዘርፉ በዚሁ ወቅት፥ ፍርድ ቤቱ በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለውን የካፒታል ገበያ የሕግ መዋቅር ለማጠናከርና በዘርፉ የሚነሱ ክርክሮችን በብቃት ለመዳኘት የሚያስችል ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም በዘርፉ የሚነሱ ክርክሮችን በብቃት ለመዳኘት የሚያስችል ለዳኞች እና ለሕግ ባለሙያዎች የካፒታል ገበያ መፅሐፍ( Guide Book) መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
መፅሐፉ ሶስት ዋና ዋና ግቦችን ማንገቡን ተናግረው፥ ከዚህ ውስጥ በካፒታል ገበያ ዙሪያ ያሉ ውስብስብ የቴክኒክና የሕግ ቃላትን ዳኞችና ጠበቆች በተመሳሳይ መልኩ እንዲረዱና አንድ ወጥ የሕግ ቋንቋ እንዲጠቀሙ ማስቻል ይጠቀሳል ብለዋል።
በገበያ ተሳታፊዎች የሚነሱ ክርክሮች በምን ዓይነት የሕግ አመክንዮ ሊፈቱ እንደሚችሉ አስቀድመው እንዲያውቁ በማድረግ በገበያው ላይ እምነት እንዲገነባ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
ለዳኞችና ለሕግ ባለሙያዎች እንደ ተግባራዊ ማስተማሪያ በመሆን ቀጣይነት ያለው ስልጠና ለመስጠት እንደሚያገለግል ተናግረዋል።
እንደ ገበያው ዕድገትና እንደ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መምጣት አጋዥ መፅሐፉ በየጊዜው እንደሚከለስና እንደሚሻሻልም አረጋግጠዋል።
የኤፍ.ኤስ.ዲ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ሂክመት አብደላ በበኩላቸው፥ የመፅሐፉ መዘጋጀት በኢትዮጵያ እየተገነባ ባለው የካፒታል ገበያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ፍላጎት የሚመልስ ተግባራዊ እርምጃ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ይህም በዘርፉ ላይ የሚሳተፉ ዳኞች እና የሕግ ባለሙያዎች ስለ ካፒታል ገበያ ያላቸውን የቴክኒክ ጽንሰሀሳቦች፣ የቁጥጥር መዋቅሮች እና የሕግ መስፈርቶች ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ያስችላል ብለዋል።
በሕግ ትርጓሜ ላይ ወጥነት እንዲኖር እና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።