ቀጥታ፡

የመጀመሪያው ተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሁለት ሳምንታት ውስጥ አገልግሎት ይጀምራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡-የመጀመሪያው ተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሁለት ሳምንታት ውስጥ የሙከራ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስጀመር እየተሰራ ስለመሆኑ በቅርቡ የ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት አፈጻጸምን ለምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት መግለጻቸው ይታወቃል።

የፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አንተነህ ማሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአንድ ማዕከል መሶብ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

የመሶብ አገልግሎት በጊዜና በቦታ ሳይገደብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ማዕከላት ቁጥር 100 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሆኖም ይሄ በቂ ባለመሆኑ ለሁሉም ማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ነው ያብራሩት።

በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የሙከራ ትግበራ እንደሚጀመር ነው የገለጹት።

በተለይም የመሰረተ ልማቶች ተደራሽነት ዝቅተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች ‘ኪዮስክ ቤዝድ’ አገልግሎት ለመስጠት ጥናት እየተካሄደ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በ8 ተቋም 41 አገልግሎት በመስጠት የተጀመረ መሆኑን አንስተው፤ በአሁኑ ወቅት በ23 ተቋም 187 አገልግሎቶች እየተሰጡ ነው ብለዋል።

በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ተቋማትን ወደ 25 በማሳደግ 250 አገልግሎቶችን ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱንም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓም ስራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም