ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም የቡና ገበያ ያላትን ተወዳዳሪነት ወደ ላቀ ደረጃ እያሳደገች ነው-‎የዓለም አቀፍ የቡና ድርጅት

አዲስ አበባ፤የካቲት 10/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በቡና ዘርፍ  እያስመዘገበች ያለው የምርትና የኤክስፖርት ዕድገት ሀገሪቱን በዓለም ገበያ ውስጥ ያላትን ተጽዕኖና ተወዳዳሪነት ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ መሆኑን ዓለም አቀፍ ተቋማትና ገዢዎች ገለጹ።

‎የዓለም አቀፍ የቡና ድርጅት (ICO) ዋና ዳይሬክተር ቫኑሲያ ኖጌራ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ እጅግ ድንቅና ጣፋጭ የሆኑ የቡና ዝርያዎች መገኛ ናት።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ዘርፉን በሙያዊ ብቃት ለመምራት የምታደርገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በገጠር የሚከናወነውን የምርት ሂደት ከዲጂታል የግብይት ሥርዓቱ ጋር መቀናጀቱ ለስኬቱ ቁልፍ ምክንያት መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

‎ወጣቶች በባህላዊ እርሻ ላይ ብቻ ሳይወሰኑ በዘመናዊ የቡና ዝግጅትና የኤክስፖርት ስራ ላይ በስፋት መሰማራታቸውንም አድንቀዋል።

‎ባጠቃላይ የዘርፉ አመራር ከጥራትና ከአስተሳሰብ ለውጥ ጋር ተዳምሮ ለኢኮኖሚ ስኬቱ መንገድ መክፈቱን ተናግረዋል።

‎በቡና ኤክስፖርትና ኢምፖርት ንግድ ላይ የተሰማሩት  ቻይናዊዋ  ኤሚሊ ዪፕ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ቡና በቻይና ደንበኞች ዘንድ ያለው ተወዳጅነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል።


 

የቡናው ልዩ  ጣዕም እና  አስደናቂ መዓዛው ለየት ያለ ተመራጭነት እንዲኖረው አድርጎታል ብለዋል።

‎ይህንንም ተከትሎ ቻይና ከኢትዮጵያ የምታስገባው የቡና መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮልድ ቲዩን አፍሪካ መስራች ማቲ ጉላሊ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ቡና ከሌሎች ሀገራት የሚለየው ሌላኛው ጉዳይ በእያንዳንዱ ክልል የሚገኙ የዝርያዎች ብዝሃነት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቀጣይ ከኢትዮጵያ ላኪዎች ጋር ሰፊ የንግድ ውይይት በማድረግ የንግድ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም