ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ሩዋንዳ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር እየተጠናከረ መጥቷል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያና ሩዋንዳ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን በኢትዮጵያና ጂቡቲ የሩዋንዳ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር፣ በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የሩዋንዳ ቋሚ መልዕክተኛ ቻርለስ ካሮምባ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በሩዋንዳ የእርስበርስ ግጭትወቅት ወታደራዊ ልዑክ በማሰማራት ለሩዋንዳ ሰላምና መረጋጋት ገንቢ ሚና መወጣቷን አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አውስተዋል።

ይህም የኢትዮጵያ አበርክቶ የሁለቱን ሀገራት ጥልቅ ወዳጅነት ያሳያል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያና ሩዋንዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ኤምባሲዎችን ከመክፈት ያለፈ መሆኑን ገልጸው፤ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን በማቋቋም ተቋማዊ መሰረት ያለው ዘላቂ ወዳጅነት ፈጥረዋል ብለዋል፡፡

የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ጠንካራ አጋርነት እየፈጠረ መሆኑንም አመላክተዋል።


 

በጤና፣ የቤት ግንባታና ከተማ ልማት መስኮች አጋርነታቸውን ለማጠናከር የጋራ መግባባት መድረሳቸውን ገልጸው፤ የሩዋንዳ የሕክምና ተማሪዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የስፔሻሊቲና ሰብስፔሻሊቲ ዘርፎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን አብራርተዋል።

ሀገራቱ በወታደራዊ ዘርፍም በጋራ እየሠሩ መሆኑን አንስተው፤ ይህንንም ተከትሎ የሥልጠናና የልምድ ልውውጥ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሩዋንዳ አቻቸው ጄኔራል ሙባረክ ሙጋንጋ ጋር የሀገራቱን ወታደራዊ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ የልምድ ልውውጦችና ውይይቶች ማድረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያና ሩዋንዳ መካከል የተገነባው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስፋት አጋርነታቸውን ማጠናከር እንደሚያስችልም አስረድተዋል።
 
 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ በቀን ሦስት ጊዜ የቀጥታተ በረራ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ይህም የሀገራቱን ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያጠናክራል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገራት መካከል መሆኗን ጠቅሰው፤ ለዚህም የአዲስ አበባ አስደናቂ የኮሪደር ልማትማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም