በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ አስተዳደር ከ46 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ወስደዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ አስተዳደር ከ46 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ወስደዋል
ጎዴ ፤የካቲት 10/2018(ኢዜአ)፡- በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ አስተዳደር ከ46 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መውሰዳቸውን የከተማው ከንቲባ አብዱላሂ አሊ ሃጂ ገለፁ።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለዜጎች ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያረጋግጥ፣ አካታች እና ደህንነቱ የተጠበቀ የመታወቂያ ስርአት ነው።
መታወቂያው ተአማኒነትን፣ አካታችነትን፣ ግልጽነትን እና መልካም አስተዳደር መርህ አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ከመንግስት የመቶ በመቶ እቅዶች አንዱ ነው።
በሶማሌ ክልል የጎዴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አሊ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአስተዳደሩ ስር የሚገኙ ነዋሪዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝግበው እንዲወስዱ የተከናወኑት ተግባራት ስኬታማ ናቸው።
በዚህም ከ46 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት መሆናቸውንም ነው የሚገልጹት።
ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ለግለሰብም ሆነ ለሀገር ደሕንነት የጎላ ፋይዳ ያለው መሆኑን በመገንዘብ ነዋሪዎች መታወቂያዉን እንዲወስዱ ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ መደረጉ ከዚህ በፊት ከመታወቂያ ካርድ ጋር ተያይዞ ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ለማቃለል እያስቻለ እንደሚገኝም አክለዋል።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም እንደ ሀገር ለተጀመሩ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ለማሳካት፣ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ የጎላ ሚና እንዳለውም ነው የገለጹት።
ከዚሁ ጎን ለጎንም በከተማ አስተዳደሩ 8 ሺህ 803 ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እድል ተጠቃሚ መሆናቸውንም ነው ከንቲባው የገለጹት።
ስልጠናው ዜጎች በዲጂታል ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ፣የስራ እድል እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ዜጎች ከቴክኖሎጂ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ ነው ያነሱት።