ኢትዮጵያ በውኃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ለአህጉራዊ አጀንዳ መሳካት መሠረት ናቸው - ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በውኃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ለአህጉራዊ አጀንዳ መሳካት መሠረት ናቸው - ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በውኃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ለአህጉራዊ አጀንዳ መሳካት ትልቅ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 መካሄዱ ይታወቃል፡፡
ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አፍሪካ በውኃ ሀብት የታደለች ብትሆንም፣ አሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ የመጠጥ ውኃ ሽፋንና የኃይል አቅርቦት ያላት አህጉር መሆኗን ጠቁመዋል።
የ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በውኃ እና ሳኒቴሽን ላይ አተኩሮ መካሄዱ ለአህጉሪቱ ወቅታዊና ዘላቂ ፍላጎትን ለማሳካት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ መሪ ሀሳብ አባል ሀገራት የውኃ ሀብታቸውን ለኢኮኖሚ ሽግግርና ለሕዝባቸው ደኅንነት እንዲያውሉ ትልቅ መነቃቃት እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በውኃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ለአህጉራዊ አጀንዳ መሳካት ትልቅ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በመንግሥት ቀጥተኛ በጀትና በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ባከናወነቻቸው ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቧን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ከስኬቶቹ መካከልም እስካሁን 80 ሚሊዮን የሚጠጋውን የሀገሪቱን ሕዝብ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ማድረግ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት ዋነኛ መነሻ የውኃ ሀብት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዚህ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ በየዓመቱ የሕብረቱን መሪዎች እያስገረመች የምትገኝ ከተማ መሆኗን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በተለይ በከተማዋ የተከናወኑ የውኃና ሳኒቴሽን ሥራዎች በመሬት ላይ የሚታዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከንግግር ባለፈ በተግባር እያሳየች ያለችው ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ትልቅ ትምህርትና ተሞክሮ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።