ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት በአምቦ ከተማ ከ9 ሺህ ለሚልቁ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል

አምቦ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት ከ9 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የአምቦ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ክኅሎት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የሥራ ዕድሉ የተፈጠረው በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በኮንስትራክሽን እና ሌሎችም መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ እሸቱ አበራ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩት ወጣቶች 20 ሺህ 554 ሔክታር መሬት እንዲሁም በአገልግሎት ለተሰማሩት ለመሥሪያና ለመሸጫ የሚሆኑ 37 ሼዶች ተገንብተው መተላለፋቸውን አብራርተዋል።
 
ከሥራ ፈጠራው ጎን ለጎን ለ591 ኢንተርፕራይዞች 156 ሚሊየን ብር የገበያ ትሥሥር መፈጠሩንም ጠቁመዋል።

የሥራ ዕድል የተመቻቸላቸው ወጣቶችም እስካሁን ከ318 ሚሊየን ብር በላይ በባንክ መቆጠባቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ለ13 ሺህ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም