ቀጥታ፡

የአፋር ክልልን ተፈጥሯዊ ፀጋ በመጠቀም ስንዴን በስፋት የማልማቱ ሥራ ቀጥሏል

ሠመራ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል ያለውን ሰፊ ለም መሬትና የውኃ አማራጮች በመጠቀም ስንዴን በስፋት የማልማቱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የስንዴን ምርታማነት ለመጨመርም ለአካበቢው የአየር ሁኔታ የተመቸ የዘር ማላመድ ሥራ በሰርቶ ማሳያና በከፊል አርብቶ አደሮች ማሳ ላይ በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ነው በቢሮው የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አሕመድ አሚን የገለጹት።


 

በዚህም መሠረት በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 1 ሺህ 442 ሔክታር ላይ ዝርያን የማላመድ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ለኢዜአ አረጋግጠዋል።


 

ይህም የዘር አቅርቦትን በራስ ዐቅም ለመሸፈንና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘው ግብ እንዲሳካ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አመላክተዋል።

ከስንዴ ምርት ባለፈ ሱፍና ሩዝን በሰፊው በማላመድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የግብዓት አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ ሃሩን አሊ በበኩላቸው፤ የስንዴ ዘር ብዜት ከማካሄድ ባለፈ በማዳበሪያና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች አቅርቦት ረገድ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
 



የስንዴ ዘርን በማላመድ ሥራ ለ15 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ያስታወቁት ደግሞ በቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር ሃመዱ መሐመድ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም